እግዚአብሔርን መስማትና መምሰል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
... ከባለፈው የቀጠለ...
ክፍል ሁለት
..."የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ"... ዮሐ 2፥5
... ሙሉ ንባቡን ስናነብ እንደምንረዳው ይህንን ትዕዛዝ ስለተቀበሉ ከችግራቸው ወጡ እንደውም ከነበራቸው በላይ አገኙ።
...መስማት ያለባቸውን ድምጽ አላወቁም ነገር ግን አክብረው መጥራት ያለባቸውን ያውቁ ነበር...በዚያ በጭንቅ ሰዓት እነርሱ አክብረው ወደ ቤታቸው የጠሯት ድንግል ማርያምን እርሷ ደግሞ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሰሙ ነገረቻቸው ... እነሱም ሰሙ የድርሻቸውንም ተወጡ... እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው ድንግል ማርያም ያረገችውን እንድናስበው ነው... እርሷን አብረው ሰሙ እርሷ ደግሞ ክርስቶስን እንዲሰሙ ምክራዊ ትዕዛዝ ሰጠቻቸው... ማንኛችንም ቢሆን መስማት አክብረን ወደ ልባችን ማስገባት ያለብን ኢየሱስ ክርስቶስንንና ወደ እርሱ የሚያደርሰንን ድምጽ ብቻ መሆን አለበት። የምናማክረውን ሰው ወደ ሕይወታችን የምንጠራውንም ሰው መምረጥ ማውቅ አለብን
.... ከሰርገኞቹ ይህ ነው የምንማረው አክብረው የጠሯት ድንግል ማርያም ከውርደት አዳነቻቸው ከውርደት ብቻ ሳይሆን ወደ ሕይወት ጠራቻቸው፣ አደረሰቻቸው፣ አስተማረቻቸውም መስማት ያለባችሁ ድምጽ አለ እርሱም የሕይወት ባለቤት የሕይወት ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱን ስሙት የሚላችሁንም ሁሉ በእምነት አድርጉ አለቻቸው...
...እርሱስ ምን አዘዛቸው? ...ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው... ይህ ቀላል ትዕዛዝ ውሃ በርሃ ላይ ካልሆነ በቀር የትም በነጻ ይገኛል። በጊዜው ግን ወደ ጋኖቹ ለመሙላት መመላለሱ ወደ ወንዝ መጓዙ እነርሱን የእርሱን እርዳት መፈለጋቸውን የሚታይበት መንገድ ነበር... እርዳታውን ስለፈለጉ ሰሙት ... ከዛም ቀድታችሁ ለአሳዳሪ ስጡት ተባሉ አደረጉትም...
የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ ቀላል ነው ሁሌም ይቻላል ግን የእኛን የማድረግ ፈቃድ ይጠይቃል በማስገደድ ምንም አያደርግልንም።
እኛም አሁን በሕይወታችን በቤታችን በደስታችን ማንን ነው በክብር የምንጠራው? በችግራችንስ በሀዘናችንስ ሰዓት የማንን ድምጽ ነው የምንሰማው?
... ኢየሱስ ክርስቶስንና ወደ እርሱ የሚያደርሱ ድምጾችን ስንሰማ የአምላካችን ክብር ይገለጻል፤ እምነታችንም ይጸናል... ስለዚህ እርሱ ሲናገር እምነታችን ያድጋል እምነታችን ሲያድግ እርሱን መስማት ብቻ ሳይሆን እርሱን መምሰልም እንጀምራለን።
...ወደ መነሻ ሀሳባችን እንመለስና ድንግል ማርያም በሰርገኖቹ ምሳሌ መሰረት..የነገረችን የመከረችን እርሱ የሚለንን ለመስማት ብቻ ሳይሆን ማድረግም እንዳለብን ነው... ይህንን ለማድረግ ደግሞ ትንሽም ቢሆን እምነት ይጠይቃል...
... እዚህ ጋር ለምንድን ነው የምናምነው? ...ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ጥያቄ መሆን አለበት። ቤተሰቦቻችን ስላወረሱን ወይስ የክርስትናው ሀሳቡ ገብቶን?
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ ላይ ያደረገልንስ ውለታ በእርግጥ ገብቶናል?
... እስቲ አሁንም እራሳችንን እንጠይቅ እግዚአብሔር ምን ያህል ይወደናል?... እኛስ ምን ያህል እንወደዋለን? .... መውደዳችንን በምን እንገልጸዋለን?....
"በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምን ዘንድ፥ ትዕዛዝንም እንደሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።" 1ዮሐ 3፥ 23
.....ትዕዛዙን በመጠበቅ ፍቅሩን እንገልጸዋለን፤ ...ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባህሪ ልጅ ነው ብለን ስናምን ደግሞ የልጅነት ስልጣንን እናገኛለን... አባታችን ብለን የምንጣራበትንም ጉልበት እንዲሁ እናገኛለን የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ እንቀበላለን ዘላለማዊ ሕይወትንም እንወርሳለን... ተመስገን...
ሁላችንም የእግዚአብሔርን መውደድ የምንገልጸው እኛ ለሌሎች ባለን የፍቅር መጠን ነው.... እምነት ማለት ደግሞ በፍቅር ውስጥ ያለ መገዛት መታዘዝ ሙሉ ማንነትን መስጠት ነው... ስለዚህ ፍጹም ፍቅር ደግሞ ፍጹም እምነትን ያመጣልናል። እግዚአብሔር ፍቅር ነውና... ፍቅር ካለን ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ሁሉም ነገር አለን ማለት ነው።
...እናስተውል እግዚአብሔር ሁሌም ይናገረናል ከመናገርም አልፎ የልባችንን በር ያንኳኳል
"እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለው እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።" ራዕ 3፥ 20
.... የልባችን በር ሲንኳኳ እነሆ አምላካችንን ድምጽ በውጭ አለ ... ሸክማችሁ የከበዳችሁ ኑ ወደኔ ላሳርፋችሁ ... ኑሮ የከበዳችሁ ችግር ላይ ያላችሁ ሁሉ ኑ ወደኔ ላሳርፋችሁ ይለናል። በውጭ ያንኳኳል ድምጹን ሰምትን ስንከፍት ግን ወደ ቤታችን ይገባል ስራውን ይጀምራል... ሸክም ችግር ኑሮ ሁሉም ይቀላሉ... "ልትድን ትወዳለህን? " ዮሐ 5፥6። ነውና ጥያቄው ማንኛችንም ድምጹን ስንሰማ ፈቅደን የልባችንን በር እንከፍትለታለን እርሱም ወደኛ ይገባል። ......ይቀጥላል.....
... ኦ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
በኃጢአት ብዛት ባክኜ የሕይወት መሰረት የሆነውን የልጅሽን ድምጽ መስማት አልቻልኩምና እባክሽን እኔንም በጭንቅ ወቅት የልጅሽን ድምጽ እሰማ ዘንድ እርጂን... ወደ ሕይወቴ በክብር አስገብቼሻለሁና....
....ዲያቆን ብልሃት በላይ
.... ግንቦት 21 2008 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment