Tuesday, May 24, 2016

"እግዚአብሔርን መስማትና መምሰል" ክፍል አንድ ከዲያቆን ብልሃት በላይ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
..አዳም ዘላለማዊ ህይወትን ፍለጋ የአምላኩን ድምፅ ትቶ የእባብን ድምፅ ሰማ።  ... ዘላለማዊነት ሊመጣ ቀርቶ... ሞት በፍጥነት መጣ...ሰው መሆንም ቀረ... መንፈስ ቅዱስ  ራቀ.... ደስታ በሀዘን፤ ህይወት በሞት፤  ጌትነት በባሪያነት፤  ተተኩ።
...በአምላክና በኛ በሰዎች መሀከል ጸብ ነገሰ።  ... ሀዘን ደስታን፤  ባርነት እረፍትን፤ ጥላቻ ፍቅር...  ይሸፍኑ ዘንድ አዳም አባታችን ለመነ... ልመናውም በፍጹም ፍቅር ነበርና እግዚአብሔርን ሳበው...  የአዳም ስህተት እንባውን (ንስሐን)፤  እንባው  (ንስሐው) ደግሞ አምላካችንን  ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ አደረጉን።
... የምህረት ቃል ተገባልን የመዳናችን ቀን በቀጠሮ ተያዘ።
....ነገር ግን እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በብዙ መልኩ ሲያናግር እያናገርም ኖረ። ...በነቢያት ተናግሯል፤  በሀዋርያት ተናግሯል ...  ይህ ሁሉ ለለውጥ መጀመሪያ  ነውና... እራሱ በባህሪ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኑ ሲደርስ እንደቃሉ ለኛ ተገለጠልን። ...የሕይወትንም  መንገድ አሳየን... ለዘላለም ማያስርበውን የሕይወትን መብልና መጠጥ ሰጠን። እንዴት መኖር፣ እንዴት መስራትና እንዴት መራመድ እንዳለብን አሳየን። ...በእኛም ላይ ለማደር ዳግም ቅዱስ መንፈሱን ላከልን...
.....እኛ ግን አሁንም ይህንን ትልቅ ነገር ቸል ብለን ዳግም የቀደመውን ጠላታችን  ድምፅ እንሰማለን። በጭንቅ ሰዓት፣  በደስታ ሰዓት፣ በሀዘን ሰዓትና በብዙ ችግር ሰዓት  ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ መስማት ያለብንን መመልከት ያለብንን የህይወት መንገድ መብል እንረሳለን።
... ለዛም ነው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  በጭንቅ ሰዓት ልጇ መልስ አለውና  በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት " እርሱን ስሙት" ያለችው.... ዳግም በደብረ ታቦር የባህሪ አባቱ ለ3ቱ ሀዋርያት በደስታቸው ሰዓት የጠየቁትን አላወቁም እና  "እርሱን ስሙት" ... ያላቸው።
...እርሱ  ኢየሱስ  ክርስቶስን መስማት ማለት ደግሞ ከላይ እንዳየነው እርሱን የሕይወታችን መመሪያ መንገድ አድርገን ማየት መቀበል ማለት ነው።
  ...አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን  መስማት ማለት እርሱን መምሰል ማለት ነው ። እርሱን ከመሰልን ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን  እንደነገሩን ከመለኮቱ ክብር ተካፋይ እንሆናለን።
... በእርሱም ስላመንን ደግሞ በአባታችን አዳም በኩል  የተቀበልነው ባርነት ቀረልን... ልጆቹ ተባልን... መአዛችንም ፍጹም ለወጠልን...  እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለናልና....
...ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ ምን አለን እኔ ክርስቶስን መስያለውና እናንተም እኔን ምሰሉ...  ክርስቶን መምሰል ምነኛ መታደል ነው።
....አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምንድን አለን?
ይህ ነው የጥያቄያችን ርዕስ መሆን ያለበት ምክንያቱም ይህንን ክብር ለመውረስ እርሱን መምሰል አለብን እርሱን ለመምሰል ደግሞ እርሱን መስማት አለብንና።
      ...ይቀጥላል...

... አምላኬ ሆይ በሕይወቴ ሁሉ አንተን እመስልህ ዘንድ በሕይወቴም የአንተን ስራ ብቻ እፈጽም ዘንድ እርዳኝ...
      ዲያቆን ብልሀት በላይ
       ግንቦት 16

No comments:

Post a Comment