Saturday, May 28, 2016

"እግዚአብሔር መስማትና መምሰል" ክፍል ሁለት ከዲያቆን ብልሃት በላይ

እግዚአብሔርን መስማትና መምሰል 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
... ከባለፈው የቀጠለ...
ክፍል ሁለት 
..."የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ"...  ዮሐ 2፥5     
... ሙሉ ንባቡን ስናነብ  እንደምንረዳው ይህንን ትዕዛዝ ስለተቀበሉ ከችግራቸው ወጡ እንደውም ከነበራቸው በላይ አገኙ። 
...መስማት ያለባቸውን ድምጽ አላወቁም ነገር ግን አክብረው መጥራት ያለባቸውን ያውቁ ነበር...በዚያ በጭንቅ ሰዓት እነርሱ አክብረው ወደ ቤታቸው የጠሯት  ድንግል ማርያምን  እርሷ ደግሞ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሰሙ ነገረቻቸው ... እነሱም ሰሙ የድርሻቸውንም ተወጡ... እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገው ድንግል ማርያም ያረገችውን እንድናስበው ነው...  እርሷን አብረው ሰሙ እርሷ ደግሞ ክርስቶስን እንዲሰሙ ምክራዊ ትዕዛዝ ሰጠቻቸው... ማንኛችንም ቢሆን መስማት አክብረን ወደ ልባችን ማስገባት ያለብን ኢየሱስ ክርስቶስንንና ወደ እርሱ የሚያደርሰንን ድምጽ ብቻ መሆን አለበት። የምናማክረውን ሰው ወደ ሕይወታችን የምንጠራውንም ሰው  መምረጥ ማውቅ አለብን 
.... ከሰርገኞቹ ይህ ነው የምንማረው አክብረው የጠሯት ድንግል ማርያም ከውርደት አዳነቻቸው ከውርደት ብቻ ሳይሆን ወደ ሕይወት ጠራቻቸው፣ አደረሰቻቸው፣ አስተማረቻቸውም መስማት ያለባችሁ ድምጽ አለ እርሱም የሕይወት ባለቤት የሕይወት ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱን ስሙት የሚላችሁንም ሁሉ በእምነት አድርጉ አለቻቸው...  
...እርሱስ ምን አዘዛቸው? ...ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው... ይህ ቀላል ትዕዛዝ ውሃ በርሃ ላይ ካልሆነ በቀር የትም በነጻ ይገኛል።  በጊዜው ግን ወደ ጋኖቹ ለመሙላት መመላለሱ ወደ ወንዝ መጓዙ እነርሱን የእርሱን እርዳት መፈለጋቸውን የሚታይበት መንገድ ነበር... እርዳታውን ስለፈለጉ ሰሙት ... ከዛም ቀድታችሁ ለአሳዳሪ ስጡት ተባሉ አደረጉትም...
የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ ቀላል ነው ሁሌም  ይቻላል ግን የእኛን የማድረግ ፈቃድ ይጠይቃል በማስገደድ ምንም አያደርግልንም። 
እኛም አሁን በሕይወታችን በቤታችን በደስታችን ማንን ነው በክብር የምንጠራው? በችግራችንስ በሀዘናችንስ  ሰዓት የማንን ድምጽ ነው የምንሰማው? 
... ኢየሱስ ክርስቶስንና ወደ እርሱ የሚያደርሱ ድምጾችን ስንሰማ የአምላካችን ክብር ይገለጻል፤ እምነታችንም ይጸናል... ስለዚህ እርሱ ሲናገር እምነታችን ያድጋል እምነታችን ሲያድግ እርሱን መስማት ብቻ ሳይሆን እርሱን መምሰልም እንጀምራለን።
...ወደ መነሻ ሀሳባችን እንመለስና ድንግል ማርያም በሰርገኖቹ ምሳሌ መሰረት..የነገረችን የመከረችን እርሱ የሚለንን ለመስማት ብቻ ሳይሆን ማድረግም እንዳለብን ነው... ይህንን ለማድረግ ደግሞ ትንሽም ቢሆን እምነት ይጠይቃል... 
... እዚህ ጋር ለምንድን ነው የምናምነው? ...ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ጥያቄ መሆን አለበት። ቤተሰቦቻችን ስላወረሱን ወይስ የክርስትናው ሀሳቡ ገብቶን?
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ ላይ  ያደረገልንስ ውለታ በእርግጥ ገብቶናል? 
... እስቲ አሁንም እራሳችንን እንጠይቅ እግዚአብሔር ምን ያህል ይወደናል?... እኛስ ምን ያህል እንወደዋለን? ....  መውደዳችንን በምን እንገልጸዋለን?.... 
   "በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምን ዘንድ፥ ትዕዛዝንም እንደሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።" 1ዮሐ 3፥ 23 
.....ትዕዛዙን በመጠበቅ ፍቅሩን እንገልጸዋለን፤ ...ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባህሪ ልጅ ነው ብለን ስናምን ደግሞ የልጅነት ስልጣንን እናገኛለን... አባታችን ብለን የምንጣራበትንም ጉልበት እንዲሁ እናገኛለን የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ እንቀበላለን ዘላለማዊ ሕይወትንም እንወርሳለን... ተመስገን...
ሁላችንም የእግዚአብሔርን መውደድ የምንገልጸው እኛ ለሌሎች ባለን የፍቅር መጠን ነው.... እምነት ማለት ደግሞ  በፍቅር ውስጥ ያለ መገዛት መታዘዝ ሙሉ ማንነትን መስጠት ነው... ስለዚህ ፍጹም ፍቅር ደግሞ ፍጹም እምነትን ያመጣልናል።  እግዚአብሔር ፍቅር ነውና... ፍቅር ካለን ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ሁሉም ነገር አለን ማለት ነው። 
...እናስተውል እግዚአብሔር ሁሌም ይናገረናል ከመናገርም አልፎ የልባችንን በር ያንኳኳል 
       "እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለው እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።" ራዕ 3፥ 20
.... የልባችን በር ሲንኳኳ  እነሆ አምላካችንን ድምጽ በውጭ አለ ... ሸክማችሁ የከበዳችሁ ኑ ወደኔ ላሳርፋችሁ ... ኑሮ የከበዳችሁ ችግር ላይ ያላችሁ ሁሉ ኑ ወደኔ ላሳርፋችሁ ይለናል።  በውጭ ያንኳኳል ድምጹን ሰምትን  ስንከፍት ግን ወደ ቤታችን ይገባል ስራውን ይጀምራል... ሸክም ችግር ኑሮ ሁሉም ይቀላሉ...    "ልትድን ትወዳለህን? " ዮሐ 5፥6።   ነውና ጥያቄው ማንኛችንም ድምጹን ስንሰማ ፈቅደን የልባችንን በር እንከፍትለታለን እርሱም ወደኛ ይገባል።   ......ይቀጥላል.....

... ኦ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
በኃጢአት ብዛት ባክኜ የሕይወት መሰረት የሆነውን የልጅሽን ድምጽ መስማት አልቻልኩምና እባክሽን እኔንም በጭንቅ ወቅት የልጅሽን ድምጽ እሰማ ዘንድ   እርጂን... ወደ ሕይወቴ በክብር አስገብቼሻለሁና....

      ....ዲያቆን ብልሃት በላይ
       .... ግንቦት 21 2008 ዓ.ም.

Tuesday, May 24, 2016

"እግዚአብሔርን መስማትና መምሰል" ክፍል አንድ ከዲያቆን ብልሃት በላይ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
..አዳም ዘላለማዊ ህይወትን ፍለጋ የአምላኩን ድምፅ ትቶ የእባብን ድምፅ ሰማ።  ... ዘላለማዊነት ሊመጣ ቀርቶ... ሞት በፍጥነት መጣ...ሰው መሆንም ቀረ... መንፈስ ቅዱስ  ራቀ.... ደስታ በሀዘን፤ ህይወት በሞት፤  ጌትነት በባሪያነት፤  ተተኩ።
...በአምላክና በኛ በሰዎች መሀከል ጸብ ነገሰ።  ... ሀዘን ደስታን፤  ባርነት እረፍትን፤ ጥላቻ ፍቅር...  ይሸፍኑ ዘንድ አዳም አባታችን ለመነ... ልመናውም በፍጹም ፍቅር ነበርና እግዚአብሔርን ሳበው...  የአዳም ስህተት እንባውን (ንስሐን)፤  እንባው  (ንስሐው) ደግሞ አምላካችንን  ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ አደረጉን።
... የምህረት ቃል ተገባልን የመዳናችን ቀን በቀጠሮ ተያዘ።
....ነገር ግን እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በብዙ መልኩ ሲያናግር እያናገርም ኖረ። ...በነቢያት ተናግሯል፤  በሀዋርያት ተናግሯል ...  ይህ ሁሉ ለለውጥ መጀመሪያ  ነውና... እራሱ በባህሪ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኑ ሲደርስ እንደቃሉ ለኛ ተገለጠልን። ...የሕይወትንም  መንገድ አሳየን... ለዘላለም ማያስርበውን የሕይወትን መብልና መጠጥ ሰጠን። እንዴት መኖር፣ እንዴት መስራትና እንዴት መራመድ እንዳለብን አሳየን። ...በእኛም ላይ ለማደር ዳግም ቅዱስ መንፈሱን ላከልን...
.....እኛ ግን አሁንም ይህንን ትልቅ ነገር ቸል ብለን ዳግም የቀደመውን ጠላታችን  ድምፅ እንሰማለን። በጭንቅ ሰዓት፣  በደስታ ሰዓት፣ በሀዘን ሰዓትና በብዙ ችግር ሰዓት  ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ መስማት ያለብንን መመልከት ያለብንን የህይወት መንገድ መብል እንረሳለን።
... ለዛም ነው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  በጭንቅ ሰዓት ልጇ መልስ አለውና  በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት " እርሱን ስሙት" ያለችው.... ዳግም በደብረ ታቦር የባህሪ አባቱ ለ3ቱ ሀዋርያት በደስታቸው ሰዓት የጠየቁትን አላወቁም እና  "እርሱን ስሙት" ... ያላቸው።
...እርሱ  ኢየሱስ  ክርስቶስን መስማት ማለት ደግሞ ከላይ እንዳየነው እርሱን የሕይወታችን መመሪያ መንገድ አድርገን ማየት መቀበል ማለት ነው።
  ...አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን  መስማት ማለት እርሱን መምሰል ማለት ነው ። እርሱን ከመሰልን ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን  እንደነገሩን ከመለኮቱ ክብር ተካፋይ እንሆናለን።
... በእርሱም ስላመንን ደግሞ በአባታችን አዳም በኩል  የተቀበልነው ባርነት ቀረልን... ልጆቹ ተባልን... መአዛችንም ፍጹም ለወጠልን...  እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለናልና....
...ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ ምን አለን እኔ ክርስቶስን መስያለውና እናንተም እኔን ምሰሉ...  ክርስቶን መምሰል ምነኛ መታደል ነው።
....አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምንድን አለን?
ይህ ነው የጥያቄያችን ርዕስ መሆን ያለበት ምክንያቱም ይህንን ክብር ለመውረስ እርሱን መምሰል አለብን እርሱን ለመምሰል ደግሞ እርሱን መስማት አለብንና።
      ...ይቀጥላል...

... አምላኬ ሆይ በሕይወቴ ሁሉ አንተን እመስልህ ዘንድ በሕይወቴም የአንተን ስራ ብቻ እፈጽም ዘንድ እርዳኝ...
      ዲያቆን ብልሀት በላይ
       ግንቦት 16

...በኔዘርላንድ ሀገር ውስጥ እስር ቤቶች እየተዘጉ ነው የተዘጉም አሉ ....


......ሁሉም ድርሻውን ከተወጣ እዚህም ይደረሳል...
...የገረመኝ ነገር...ግን እንዴት ሊሆን ይችላል?
ለነገሩ አፍሪካ ውስጥ ተወልጄ እንደዚህ ብጠይቅ አትፍረዱብኝ ሁሉም ጉልበተኛ ኑሮውም ጉልበቷ እኛላይ... ብቻ ይሁን... ተመስገን ነው እኛም እንበረታባታለን... የቀደሙት ፍቅርን ዘርተው አለፉ አባቶቻችን ደግሞ አጭደው በሉ  ለእኛም ሳይዘሩልን እምነትና ተስፋን ብቻ ሰጥተውን  አለፉ እኛ ይኸው በፍቅር እጦት እንራባለን በእምነት እና ተስፋ እንጓዛለን  ሁሉም እጃችን ላይ ሆኖ እንቸገራለን...  እኛስ እሺ የቀደሙት አባቶችንን ትዝታም ያጥግበን ልጆቻችንስ?
...አይደለም ከአውድማው ከነመፈጠሩ ፍቅር ስለመኖሩ ለሚጠራጠሩት? እምነት እና ተስፋ ላጡት...  እናስብበት... ለኛ ቢያልፍ ቢረፍድ እንኳን  ለልጆቻችን ለቀጣይ ትውልድ እናስብ...  ይህንን ደግሞ የሁሉም የሁላችንም ድርሻ ነው።.... እምነትና ተስፋ ከነዚህም በላይ ፍቅርን እናውርስ እንዝራ። ... ፍቅር ከሁሉም በላይ ...  የሰው ልጅ የሚበላውን ነው የሚመስለውና ፍቅርን እንመገብ ..... እናስተውል  ሁልጊዜም ከክፋት ደግነት ....ከጥላቻ ፍቅር ....ከጸብ እርቅ ....ከክርክር መስማማት ይሻላል... ወደ ራሳችን ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ ... ያኔ እስር ቤት አይደለም ፍርድ ቤት ይዘጋል....
         ....ዲ. ብልሃት በላይ
          ......ግንቦት 15 2008 ዓ.ም....

http://www.techinsider.io/dutch-prisons-are-closing-2016-3?utm_content=buffer57f40&utm_medium=social&utm_source=facebook.com&utm_campaign=buffer-ti

Monday, May 23, 2016

" ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4:20)

እግዚአብሔር ይወደናል ፍቅሩን ለመግለጽ ሁሉን ሰጥቶናል። የሰጠንንም ሁሉ ይፈልጋል እኛ ምንም ሳናጓድል ከነትርፉ ልንሰጥ ግድ ይለናል..ነገር ግን እኛ በተንኮል ተውጠን በክፋት ታስረን እርሱ በነጻ የሰጠንን እኛ በጉልበት ያገኘነው ይመስል እንጓዛለን... ንጹህ ፍቅር በነጻ ሰጠን ማስተዋልንን  ከጥበብ ጋር አደለን ሙሉ ተስፋን በእምነት ውስጥ አስቀመጠልን... እናም..... እንዲሁ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመለሳል ተብሏልና አሁንም ይመጣል እንደ ቀድሞ ለፍቅር ሊ'ቀጣ ሳይሆን ስለ ፍቅር ሊቀጣን ነው።  አዎ ሁላችንም ልንረዳው የሚገባ ነገር እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነው ፍቅር ነው ይህ የእርሱ የባህሪው መገለጫ ነው ነገር ግን ይህንን ስናጎድል ስለፍቅር እንድናስተካክለው ይለምነናል ብዙ ምርጫዎች ይሰጠናል  ካልቻልን ግን  ቅጣቱን ሊሰጥ  ይመጣል... አዎ እርስ በርስ እንድንዋደድ አንዳችን የአንዳችንን በደል እንድንሸፍን እንድንረዳዳ አዞን ሄዷልና...  የሰጠንን ጥያቄ በግልጽ  ተቀምጧል
...ተርቤ አበላችሁን? ተጠምቼ አጠጣችሁኝ ?ታርዤ አለበሳችሁኝ? ታስሬ ጠየቃችሁኝ?.... እኚህ ጥያቄዎች ስናስተውል እርሱን ከእኛ ጋር እኩል የሚያደርገው እንደውም የሚገርመው ከእኛም ትንንሾች ጋር ያስቀምጣል ከታናናሾቹ ለአንዱ ካደረጋችሁ ለእኔ እንዳደረጋችሁ ነው (ማቴ 25)... ፍቅሩ ምነኛ እጅግ ይደንቃል ሁልም ጊዜ ለእኛ  ያደላልና... 
....ኦ አምላኬ ሆይ ምነኛ እራስህን ስለፍቅር አወረድከው እራስህን አሳልፈህ ሰጠኸን ... አምላኬ ሆይ የእራሴን በደል ብቻ እያሰብኩኝ የእራሴን ሀጢያት ብቻ እየተመለከትኩኝ የምጸጸትበትን ሌላውን በችግሩ በውድቀቱ ሰዓት የምረዳበትን በመንገዱም የማግዝበትን ወደ አንተ ቤት የማቀርብበትን በችግሩ የምረዳበትን።... ስለእራሴ በደል እንጂ ስለሌላው የማላይበትን አስተዋይ ልብ ስጠኝ .... በዛ በፍርድ ሰዓት ለምጠየቅው ጥያቄ መልስ ይህ ነውና።
  .......ዲያቆን ብልሃት በላይ
  .......ግንቦት 14

" ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (የማቴዎስ ወንጌል 6:33)

ይህንን ቃል ሳነበው ሁሌም ግርም ይለኛል ምክንያቱም እራሴን እንድታዘበውና ያደርገኝና የእምነቴን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳየኛል። የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጉታል ምግብ መጠለያ ልብስ እኚህን ለሟሟላት ብሎም አልፎ ከመሰረታዊው ተጨማሪ ደስታውን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን ለማግኘት ይጥራል።
እኛ የሰው ልጆች ግን ዋናውን ትተን ጭማሪው ላይ እንለፋለን።
... ይህ ሁሉ ...ብሎ ያስቀመጠው ቃል በእርግጥ ምንድን ነው? ወደ ላይ ወጥተን ምዕራፉን ስናነበው ለሰው ልጆች መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው።
እዚህ ጋር ማወቅና መረዳት ያለብን ማንኛውም መብት ከግዴታ ጋር ነው የሚሰጠው ሁላችንም መብታችንን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንን ማወቅ አለብን። ግዴታችን ስንል ግን በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው እንጂ በጭቆና እና በኃይል አይደለም። ዋናው ቁም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግስት ለማግኘት ምን እናድርግ ነው።
.....መጀመሪያ ማመን አለብን እምነታችን ደግሞ በተግባር መገለጽ አለበት።
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እራሱ እግዚያብሔር መሆኑን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ህይወታቸው መሆኑን ማመን። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስንል ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አምላክ አለመሆናቸውን ማወቅ ማመን። ጥንት ያለአባት ከባህሪ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ መወለዱን ዳግመኛ ያለ ወንድ ዘር ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛን ለማዳን ስለ እኛ ፍቅርም ሲል መወለዱን ማመን። ዳግመኛ የእግዚአብሔርን ልጅነት የምናገኝበትን የልጅነት ጥምቀትን መጠመቅ ማመን። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ሲል በቀራንዮ አደባባይ በራሱ በአባቱ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ የሰጠውን ክቡር ስጋውና ደሙ አምኖ መቀበል። ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ አዲስ ሰማይ አዲስ ምድር እንዳለ ማመን።
እነዚህን አምነን ማድረግ ወይም ስርዓት የሚያስፈልጋቸውን ማድረግ ስርዓትም መፈጸም።
ሌላው ዋጋችንንና ቦታችንን ማወቅ ይህ ማለት ከላይ እንዳየነው በኢየሱስ ክርስቶስ እስካመንን ድረስ የእግዚአብሔር ልጆች እንጂ ባሮች እንዳልሆንን መረዳት እግዚአብሔርን አባታችን ብለን የምንጠራበት ስልጣን እንዳለን መረዳት። ሌላው ለእኛ ሲል በቀራንዮ የተከፈለውን ክፍያ ማስታወስ በደሙ እንደገዛን ማወቅ። በአምላክ ደም ነው የተግዛነው ዋጋችን ውድ ነው ምንም ሊተካው አችልም ይህንን መረዳት። ሌላው ፍቅርና ጽኑ ተስፋ ያስፈልገናል ሁሉን ብናሟላ ፍቅር ከሌለን ነገሩን በ ዜሮ እንደማባዛት መሆኑን ማወቅ ማንኛውም ነገር በዜሮ ከተባዛ ዜሮ ነውና። ፍቅር ከሁሉ በላይ መሆኑን ማመን። ለእኛ ሌሎች እንዲያደርጉ የምንመኘውን እኛም ለሌሎች እንዲሁ ማድረግ። እራሳችንን መጠበቅ ባልንጀሮቻችንንም መጠበቅ። እርስ በርስ መከባበር መፈቃቀር።
....እግዚአብሔር እራሱ ፍቅር ነውና ፍቅርን ከመስጠት ጋር እንጂ ከመቀበል ጋር አለማዛመድ ፍቅር የራሱን ለመስጠት እንጂ የሰውን ለመቀበል እንደማይፈልግ መረዳት ይህንን ደግሞ በጽኑ ተስፋ ማራመድ እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ ነውና በእምነት ተስፋ ስላደረግነው ነገር በእርግጠኝነት መኖር።
እንደገና ስለ እራሳችን በደንብ ማወቅ ሰው ስንባል ስጋ ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንንም ማሰብ እዳለብን መረዳት። ለስጋ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችም ለነፍስ እንደሚያስፈልጉ ማወቅ ለስጋ ምግብ መጠጥ እንድምናቀርበው ለነፍስም ምግብ መጠጥ ያስፈልጋል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። መጸሐፍ ቅዱስ ማንበብ ቃለ እግዚአብሔር ማዳመጥ። ለስጋ ልብስ መጠለያ እንደሚያስፈልገው ለነፍስም ልብስ የጽድቅ ስራ መጠለያ ካህናት አባቶች ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስፈልጓት ማወቅ። አባት ለልጁ ልብስ ምግብ መጠለያ እንደሚያቀርብ የነፍስ አባት ካህናት አባቶች ለነፍሳችን ምግብን ቃለ እግዚአብሔርን መጠለያን ቤተ ክርስቲያንን ያዘጋጁልናል። የአምላካችንን ስጋና ደም ይመግቡናል። ይህ ሁላ አልፎ ሰው ነንና ብንሳሳት በንስሃ ይመልሱናል። ከመውደቅ በኋላ መነሳት እንዳለም ያሳዩናል ስንደክም ማረፊያ መሸሸጊያ ይሆኑናል። የአምላካችንን የመድኋኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ይቅር ባይነት ያስተምሩናል።
ሌላኛው የይቅርታ ልብ ነው። የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል። እኛ ምንም የሚወደድ ምንም የምናቀርበው መልካም ስራ ሳይኖር በፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ ተመለከተን በፍቅር ይቅር አለን በፍቅር ሁሉንም ነገር ሸፈነልን። ስለዚህም እኛም እርሱን ልንከተል ልንመስለውም ይገባል በፍቅር ሁሉን መመልከት በፍቅር ሁሉን መሸፈን ስለፍቅር ሁሉንም ነገር መተው። ይህንን ነገር ሁላ አምነን አውቀን ተግብረን ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተጨመረልን አሁንም ከስረናልና የእርሱን ቸርነት በእምነትና በተስፋ ፍቅርን አስቀድመን መለመን።
...ይህ ነው የእግዚአብሔርን ጽድቅ መንግስት እንድናገኝ የሚረዳን ይህንን ስንፈጽም ሌሎቹ ሁሉ ይጨመሩልናል የስጋ ደስታን ከነፍስ ተነስተን ማግኛት ይቻላል የነፍስን ደስታ ግን ከስጋ ተነስተን ማግኘት አንችልምንና።
ይህንን ቃል የገባልን እራሱ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በመልክተኛም አልተነገረን ስለዚ ቃሉ ጥብቅ ነው። ደግሞ ለቃሉ ታማኝ አምላክ አለን።
...እናምናለን... ተመስገን ...
......ዲያቆን ብልሃት በላይ.....
.....ግንቦት 7....