Monday, May 23, 2016

" ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (የማቴዎስ ወንጌል 6:33)

ይህንን ቃል ሳነበው ሁሌም ግርም ይለኛል ምክንያቱም እራሴን እንድታዘበውና ያደርገኝና የእምነቴን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳየኛል። የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልጉታል ምግብ መጠለያ ልብስ እኚህን ለሟሟላት ብሎም አልፎ ከመሰረታዊው ተጨማሪ ደስታውን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን ለማግኘት ይጥራል።
እኛ የሰው ልጆች ግን ዋናውን ትተን ጭማሪው ላይ እንለፋለን።
... ይህ ሁሉ ...ብሎ ያስቀመጠው ቃል በእርግጥ ምንድን ነው? ወደ ላይ ወጥተን ምዕራፉን ስናነበው ለሰው ልጆች መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው።
እዚህ ጋር ማወቅና መረዳት ያለብን ማንኛውም መብት ከግዴታ ጋር ነው የሚሰጠው ሁላችንም መብታችንን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንን ማወቅ አለብን። ግዴታችን ስንል ግን በፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው እንጂ በጭቆና እና በኃይል አይደለም። ዋናው ቁም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግስት ለማግኘት ምን እናድርግ ነው።
.....መጀመሪያ ማመን አለብን እምነታችን ደግሞ በተግባር መገለጽ አለበት።
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እራሱ እግዚያብሔር መሆኑን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ህይወታቸው መሆኑን ማመን። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስንል ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አምላክ አለመሆናቸውን ማወቅ ማመን። ጥንት ያለአባት ከባህሪ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ መወለዱን ዳግመኛ ያለ ወንድ ዘር ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛን ለማዳን ስለ እኛ ፍቅርም ሲል መወለዱን ማመን። ዳግመኛ የእግዚአብሔርን ልጅነት የምናገኝበትን የልጅነት ጥምቀትን መጠመቅ ማመን። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ሲል በቀራንዮ አደባባይ በራሱ በአባቱ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ የሰጠውን ክቡር ስጋውና ደሙ አምኖ መቀበል። ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ አዲስ ሰማይ አዲስ ምድር እንዳለ ማመን።
እነዚህን አምነን ማድረግ ወይም ስርዓት የሚያስፈልጋቸውን ማድረግ ስርዓትም መፈጸም።
ሌላው ዋጋችንንና ቦታችንን ማወቅ ይህ ማለት ከላይ እንዳየነው በኢየሱስ ክርስቶስ እስካመንን ድረስ የእግዚአብሔር ልጆች እንጂ ባሮች እንዳልሆንን መረዳት እግዚአብሔርን አባታችን ብለን የምንጠራበት ስልጣን እንዳለን መረዳት። ሌላው ለእኛ ሲል በቀራንዮ የተከፈለውን ክፍያ ማስታወስ በደሙ እንደገዛን ማወቅ። በአምላክ ደም ነው የተግዛነው ዋጋችን ውድ ነው ምንም ሊተካው አችልም ይህንን መረዳት። ሌላው ፍቅርና ጽኑ ተስፋ ያስፈልገናል ሁሉን ብናሟላ ፍቅር ከሌለን ነገሩን በ ዜሮ እንደማባዛት መሆኑን ማወቅ ማንኛውም ነገር በዜሮ ከተባዛ ዜሮ ነውና። ፍቅር ከሁሉ በላይ መሆኑን ማመን። ለእኛ ሌሎች እንዲያደርጉ የምንመኘውን እኛም ለሌሎች እንዲሁ ማድረግ። እራሳችንን መጠበቅ ባልንጀሮቻችንንም መጠበቅ። እርስ በርስ መከባበር መፈቃቀር።
....እግዚአብሔር እራሱ ፍቅር ነውና ፍቅርን ከመስጠት ጋር እንጂ ከመቀበል ጋር አለማዛመድ ፍቅር የራሱን ለመስጠት እንጂ የሰውን ለመቀበል እንደማይፈልግ መረዳት ይህንን ደግሞ በጽኑ ተስፋ ማራመድ እግዚአብሔር ለቃሉ ታማኝ ነውና በእምነት ተስፋ ስላደረግነው ነገር በእርግጠኝነት መኖር።
እንደገና ስለ እራሳችን በደንብ ማወቅ ሰው ስንባል ስጋ ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንንም ማሰብ እዳለብን መረዳት። ለስጋ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችም ለነፍስ እንደሚያስፈልጉ ማወቅ ለስጋ ምግብ መጠጥ እንድምናቀርበው ለነፍስም ምግብ መጠጥ ያስፈልጋል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። መጸሐፍ ቅዱስ ማንበብ ቃለ እግዚአብሔር ማዳመጥ። ለስጋ ልብስ መጠለያ እንደሚያስፈልገው ለነፍስም ልብስ የጽድቅ ስራ መጠለያ ካህናት አባቶች ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስፈልጓት ማወቅ። አባት ለልጁ ልብስ ምግብ መጠለያ እንደሚያቀርብ የነፍስ አባት ካህናት አባቶች ለነፍሳችን ምግብን ቃለ እግዚአብሔርን መጠለያን ቤተ ክርስቲያንን ያዘጋጁልናል። የአምላካችንን ስጋና ደም ይመግቡናል። ይህ ሁላ አልፎ ሰው ነንና ብንሳሳት በንስሃ ይመልሱናል። ከመውደቅ በኋላ መነሳት እንዳለም ያሳዩናል ስንደክም ማረፊያ መሸሸጊያ ይሆኑናል። የአምላካችንን የመድኋኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ይቅር ባይነት ያስተምሩናል።
ሌላኛው የይቅርታ ልብ ነው። የይቅርታ ልብ ሊኖረን ይገባል። እኛ ምንም የሚወደድ ምንም የምናቀርበው መልካም ስራ ሳይኖር በፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስ ተመለከተን በፍቅር ይቅር አለን በፍቅር ሁሉንም ነገር ሸፈነልን። ስለዚህም እኛም እርሱን ልንከተል ልንመስለውም ይገባል በፍቅር ሁሉን መመልከት በፍቅር ሁሉን መሸፈን ስለፍቅር ሁሉንም ነገር መተው። ይህንን ነገር ሁላ አምነን አውቀን ተግብረን ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተጨመረልን አሁንም ከስረናልና የእርሱን ቸርነት በእምነትና በተስፋ ፍቅርን አስቀድመን መለመን።
...ይህ ነው የእግዚአብሔርን ጽድቅ መንግስት እንድናገኝ የሚረዳን ይህንን ስንፈጽም ሌሎቹ ሁሉ ይጨመሩልናል የስጋ ደስታን ከነፍስ ተነስተን ማግኛት ይቻላል የነፍስን ደስታ ግን ከስጋ ተነስተን ማግኘት አንችልምንና።
ይህንን ቃል የገባልን እራሱ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በመልክተኛም አልተነገረን ስለዚ ቃሉ ጥብቅ ነው። ደግሞ ለቃሉ ታማኝ አምላክ አለን።
...እናምናለን... ተመስገን ...
......ዲያቆን ብልሃት በላይ.....
.....ግንቦት 7....

No comments:

Post a Comment